Sunday, April 13, 2008

Ethiopian Glory of Kings translated into Hebrew by a Jewish Author Dr Ran Hakohin

ክብረ ነገሥት በእሥራኤላዊው ምሁር ዓይን
Wednesday, 09 April 2008

ዶ/ር ራን ሐኮኸን “ክብረ ነገሥት” በኢትዮጵያ ለ700 ዓመታት ያህል ብሔራዊ መተዳደሪያ ሆኖ ሲያገለግል የኖረ መጽሐፍ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የቤተ ሰለሞን ሥርወ መንግሥት (ሰሎሞናይክ ዳይናስቲ) ምንጭ ለመጀመሪያ ጊዜም የተገኘው በክብረ ነገሥት ውስጥ ነው፡፡ ንግሥተ ሳባ ኢየሩሳሌምን ጎብኝታ ከንጉሥ ሰሎሞን ጋር ስለመገናኘቷና ቀዳማዊ ምኒሊክ ስለመወለዱ ታቦተ ጽዮን ወደ አክሱም ስለመምጣቷ ይተርካል፡፡


ከ16ኛው ምእት ዓመት ወዲህ ስለ ኢትዮጵያ ነገሥታት ስለ ሥርወ መንግሥቱ የሚተረኩትን በተለያዩ የአውሮጳ አገሮች መጻፉ አልቀረም፡፡ በቅርቡ አንድ እሥራኤላዊ ምሁር ክብረ ነገሥትን ወደ እብራይስጥ ተርጉመውታል፡፡ የቀደሙትን እትሞች ስንቃኝ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ የፖርቱጋል ንጉሥ ማኑኤል ቀዳማዊ ልዩ መልዕክተኛ ሆኖ ወደ ዳግማዊ አፄ ዳዊት በመጣ ጊዜ በ1525 ዓ.ም ያየውንና የሰማውን የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ባህላዊ ገጽታዎች በተነተነበት “ዘ ፕሬስተር ጆን” በተሰኘው መጽሐፉ ስለ ኢትዮጵያ ነገሥታት መነሻ ጽፏል፡፡ ስለ ክብረ ነገሥት ተጨማሪ መረጃ የሰጠው የኢየሱሳውያን ካህን የሆነው ማኖኤል ዶ አልሜዳ “ሒስቶሪያ ደ ኢትዮጵያ” በሚባለው መጽሐፉ ነው፡፡

በ16ኛው ምእት የመጀመሪያ ሩብ ዓመታት ስለ ንጉሥ ሰሎሞንና ስለ ልጁ ምኒልክ ከክብረ ነገሥት ያገኘውን ትውፊት ፒ.ኤን ጎዲንሆ ያሳተመ ሲሆን፣ ስኮትላንዳዊው ጀምስ ብሩስ በ18ኛው ምእት ዓመት የዓባይን ምንጭ ለማሰስ በመጣ ጊዜ የአፄ ተክለሃይማኖት ዳግማዊ እንደራሴና ባለሙሉ ሥልጣን የነበሩት ራስ ሚካኤል ሥሁል ከሰጡት የብራና መጻሕፍት መካከል አንዱ ክብረ ነገሥት ነበር፡፡

ኦገስት ዲልማን የክብረ ነገሥትን ምጥን (ሰመሪ) ሲያዘጋጅ ኤፍ. ፕሬቶሪየስ 12 ምዕራፎችን (ከ19-32) ወደ ላቲን ተርጉሞ አሳትሟል፡፡ የግእዙን ክብረ ነገሥት ከትንተና ጋር ጀርመን ውስጥ በ1897 ዓ.ም(1905) ከጀርመንኛ ምጥን ትርጉም ጋር ያሳተመው ካርል ቤዞልድ ነው፡፡ የመጀመሪያው የእንግሊዝኛ ትርጉም የተከናወነው በዋሊስ በጅ አማካይነት ሲሆን ሁለት እትሞች በ1922 እና በ1932 አውጥቷል፡፡ መጽሐፉ በሩሲያኛ፣ በፈረንሣይኛም ተተርጉሟል፡፡ አሁን ደግሞ እሥራኤላዊው ዶክተር ራን ሐኮኸን ወደ እብራይስጥ ቋንቋ ሲተረጉሙት በቅርቡ ይታተማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከእርሳቸው ጋር ባደረግነው ቃለ ምልልስ፣ “ኢትዮጵያ ከእሥራኤል ጋር ስላላት ተዛምዶ የሚያስረዳውን ክብረ ነገሥት በእሥራኤል ኅብረተሰብ ዘንድ እምብዛም አይታወቅም፡፡ ይሁን እንጂ የእብራይስጥ ትርጉም ከሌሎች ይልቅ አስፈላጊ ነው፡፡ በዐውደ ንባቡ ኢትዮጵያውያን ፣እኛ ቤተ እሥራኤላውያን ነን፣ ይላሉና” ያሉት ዶክተር ሐኮኸን፣ ክብረ ነገሥትን ወደ እብራይስጥ ቋንቋ መተርጐም በእሥራኤል ለሚኖሩት ከ100,000 በላይ ቤተ እሥራኤላውያን ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

“የእሥራኤል መገናኛ ብዙኀን ስለ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ሲጽፉ የሚጠቅሱት ድህነታቸውና ባህላዊ ችግሮቻቸውን ነው፡፡ ከገጠር አካባቢ መምጣታቸውና ያልተማሩ መሆናቸው ከእስራኤል ማኅበረሰብ ጋር ለመዋሐድ ችግር እንደፈጠረባቸው ይጠቁማሉ”

በጥቁሮቹ አይሁዶች (ኢትዮጵያውያኑ) ላይ በተለይ በአክራሪ አይሁዶች የዘረኝነት ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ አጥባቂ ሃይማኖተኞቹ ከለዘብተኞቹ ይልቅ ዘረኞች ናቸው፡፡

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ክርስትና ውስጥ የአይሁድ ልማዶች መኖራቸው እንደማያውቁ የጠቀሱት እስራኤላዊው ምሁር፣ የጣና ሐይቅ በጎበኙበት ጊዜ በሐይቁ ካሉት የአሣ ዝርያዎች መካከል እንደ አይሁዶች የማይበሉ መኖራቸውን መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ምሁሩ አገላለጽ እሥራኤላውያን ለበርካታ ሺሕ ዓመታት የዘለቀውን ልዩና የበለጸገ ባህል ያላትን፣ ለየት ያለውን አፍሪካዊ ክርስትና የመሠረተችውን ኢትዮጵያን አለማወቃቸው የሚገርም ነው፡፡

ይህን ክፍተት ለመሙላት ኢትዮጵያ ከባህሏና ከአይሁዳዊነት ጋር ካላት ልዩ ተዛምዶ አንፃር ክብረ ነገሥትን ለመተርጐም ካነሳቸው ዐበይት ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ዶ/ር ሐኮኸን አስረድተዋል፡፡ ንግሥተ ሳባ በክብረ ነገሥቱ አጠራር ንግሥት ማክዳ ወደ ጠቢቡ ሰሎሞን ስላደረገችው ጉዞና በብልሃቱ እንዴት እንደተገናኛትና እንደፀነሰች አገሯ ተመልሳ ልጅዋን እንደወለደች ይተርካል፡፡

በኢትዮጵያ የንግሥና ትውፊት ውስጥ የልጁ ስም ቀዳማዊ ምኒልክ ቢሆንም በክብረ ነገሥት ውስጥ ስሙ “በይነል ሐኪም” (ኢብነ እል ሐኪም) ተብሎ ተጽፏል፡፡ ወልደ ጥበብ ማለት ነው፡፡

በይነል ሐኪም ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ከአባቱ ጋር መገናኘቱን፣ በኢትዮጵያም እንደነገሠ ቤተ ሰለሞን ሥርወ መንግሥትም መጀመሩን ያወሳል፡፡

ክብረ ነገሥት እውነተኛ ታሪክ ነው ወይስ ሌጀንድ (አፈ ታሪክ) ተብለው ለተጠየቁት ምሁሩ ሲመልሱ፣ “በቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጽሑፍ አስተምራለሁ፡፡ በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ውስጥ ታሪክ ትክክለኛ ይሁን አይሁን መሠረታዊ ነገር አይደለም፤ በክብረ ነገሥትም ቢሆን እንዲሁ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ባህላዊ ማንነትን ለበርካታ መቶ ዓመታት ቀርፆታል፡፡ ይህም ከጥያቄው በላይ በጣም ጠቃሚ የሆነ ክንውን ነው” ብለዋል፡፡

ለእሥራኤላውያን ክብረ ነገሥቱንና ታሪኩን በቋንቋቸው ማቅረብ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው፤ ኢትዮጵያውያን ቤተ እሥራኤሎችን በቅጡ ለመረዳትና አይሁዳዊ መሠረት ያለውን ክርስትና ለመገንዘብም ይረዳቸዋል፡፡

ዶ/ር ራን ሐኮኸን ያዘጋጁት የክብረ ነገሥት እብራይስጥ ትርጉም “አኖቴሽን” (መግለጫ) ያለው በመኾኑ፣ የቀደሙት ቋንቋዎች ትርጉሞች ካሏቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ግርጌ ማስታወሻ ይለያል፡፡ በክብረ ነገሥት ውስጥ የሚገኙትን የአይሁድ ምልክቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን፣ ታልሙድን ከመሳሰሉ የአይሁድ ሥነ ጽሑፎች እንደመረመሯቸው ምሁሩ ገልጸዋል፡፡

በክብረ ነገሥት የመጨረሻ ገጾች ላይ መጽሐፉ መጀመሪያ የተጻፈው በኮፕት (የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቋንቋ) መሆኑን ወደ ዐረብኛ ከተተረጐመው እትም በ14ኛው ምእት መጀመሪያ ወደ ግእዝ መተርጐሙ ተጽፏል፡፡ አብዛኞቹ ምሁራን መጽሐፉ የተደረሰው በ14ኛው ምእት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ትርጉም አይደለም፤ የአክሱም ንቡረ እድ ይስሐቅ ከስድስት ሊቃውንት ካህናት ጋር በመሆኑ ከውጭና ከሀገር ውስጥ ልዩ ልዩ መጻሕፍት በመመሥረት በግእዝ ደርሰውታል የሚል የሌሎች ወገኖች አስተያየት አለ፡፡

ዘመኑን በተመለከተ ትውልደ ዐረብ የሆኑ አሜሪካዊ በስድስተኛው ምእት መጻፉን ሲጠቅሱ፣ እንግሊዛዊው አርኪዮሎጂስትም ስለታቦተ ጽዮን ከ16ኛው ምእት በፊት የተጠቀሰበት የለም ይላሉ፡፡

ዶክተር ሐኮኸን ክብረ ነገሥት ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው በተለይ ኤድዋርዶ ዑልንዶርፍ የገለጹበትን መንገድ ይሁንታ ይሰጡበታል፡፡

“ብሉይ ኪዳን (ኦሪት) ለእሥራኤሎች፣ ወይም ቁርዓን ለዐረቦች እንዳላቸው ልዩ ስፍራ ሁሉ ክብረ ነገሥትም ኢትዮጵያ ከሥነ ጽሑፋዊው እሴት ባሻገር የኢትዮጵያ ብሔራዊ መለዮና ሃይማኖታዊ መሠረት አመልካች ነው”

የክብረ ነገሥት እብራይስጥ እትም ከሁለት ወር በኋላ እሥራኤል ውስጥ ለአደባባይ እንደሚበቃ ተርጓሚው ገልጸዋል፡፡

በሔኖክ ያሬድ

No comments: